ጸሐይ ስትጠልቅ፣ መጽሐፍ ሳገላብጥ

ጸሐይ ስትጠልቅ

ጸሐይ :-የቀድሞ ተማሪ፣ አሁን ዕድሜው ገፍቶ ከአልጃጀ በስተቀር ፣ ማንም በደንብ እንደሚያስታውሰው ” …በብርቲሽ ኢምፓየር ፣ በታላቁዋ ብርታኒያ ላይ ጸሐይ ትንከራተታለች እንጂ ምንጊዜም አትጠልቅም ” ይባላል ። አሁን ግን ጀምበር ሌላው አገር እንደምትጠልቀው ሁሉ፣ በእንግሊዝም ላይ ማታ ማታ ትሰወራለች። እዚያም ጨለማውም ነግሶ፣ እሱዋን ሲያሸብራት እናያለን። ኮከቦችንም አልፎ አልፎ አዚያ ደሴት ላይ ተቀምጦ መቁጠርም ይቻላል።

መቼም ሰሞኑን እጄ የገባው መጽሐፍ /1 አርዕሰቱ ብቻ ሳይሆን ይዘቱም ጭምር ግሩም ነው። በዚህ አመት ከአነበብኩአቸው “በርካታ/ ጥቂት” መጽሓፍቶችም ውስጥ በእርግጠኛነት ለመናገር ይህኛው አንደኛው አስደናቂ መጽሐፍ ነው።

ለምን ለአለፉት አምስት መቶ አመታት፣ ማንም ሳይቀድመንና ሳይበልጠን የዓለምን የልብ ትርታ የወሰንን ሰዎች፣ አሁን ዓይናችን እያየ የበላይነቱን ከእጃችን ተነጠቅን ? ብሎ ጸሓፊው Naill FERGUSON እራሱንም፣ አያይዞም አንባቢውንም አብሮ ይጠይቃል። በሁለት መንገድ ጸሓፊው መልስ ከመስጠቱ በፊት የአውሮፓ ሥልጣኔና አመጣጥ በምን ላይ እንደተመሰረተ ይተርካል። ቆየት ብሎም፣ እራሱ የወረወረውን ጥያቄ ወደ መመለሱም ይሸጋገራል።

“ሚስጢራችንን” (ይህን እሱ FERGUSON “Killer-Apps ,… Applications” ብሎ የሚጠቁመውን ቃል በሌላ ቋንቋ መተርጎም አቅቶኝ!) ሚስጢራችንን ሌሎቹ አድፍጠው ቀድተው፣ በሥራ ተርጉመው “እኛን ጉድ አደረጉን “፣ ይላል።

እዚህ ጀርመን መጥቶ ጸሓፊው መጽሐፉን ለማሰተተዋወቅ በአደረገው ንግግሩም ላይ፣ ነገሩን ሁሉ ሰብሰብ አድርጎት፣ እንደዚህ አድረጎ ለማወቅ ለሚፈልግ ሰው አስቀምጦታል። እናዳምጠው።

… ጃፓንና ሕንድ ፣ ብራዚልና ደቡብ ኮሪያ ፣ ቻይናም ጭምር …አሥራ አንዱ የምዕራቡ አገሮች፣ ብቻቸውን ጨብጠውት ይዘው የነበረውን “ሚስጢራዊ፣… ጥበብና ዕውቀት” ፣ እነሱ እላይ የተጠቀሱት ወጣት፣ መጤ ፣ ታዳጊ አገሮች ለቀም አድርገው ቀድተው ለእራሳቸው ጥቅም አዋሉት፣ ይላል። በዚህ ጉዞም አሁን በቅርቡ፣ አሜሪካ በቻይና (በኢኮኖሚ ዕድገት) ትቀደማለች። የዋሆች ግን በተለይ የእኛዎቹ ፣ ቻይና እዚህ የደረሰችው፣ “በሶሻሊዝም ፍልስፍና ነው” ሊሉ ይችላሉ! እውነቱ ግን እሱ ላይ አይደለም !

ለአለፉት አምስት መቶ አመታት አውሮፓ፣ የምዕራቡ ዓለም “ዓለምን ለመቆጣጠር” የቻለችው በስድስት አብይ ነገሮች ላይ ተመስርታ እንደሆነ (–ሌሎቹ ጸሐፊዎች ቀጥሩን ከፍ ያደርጉታል– ) ጸሐፊው ይጠቅሳል። ከእዚያም ውስጥ “በአራቱ ምሶሶዎች” ላይ ደህና አድርጎ ይመላለሳል።

አንደኛው፥ በእሱ ዓይን፣ “የሐሳቦችና የፈጠራዎች ፉክክር፣ ውድድር ” የሚለው ብልሃት፣ እንደሆን ይገልጻል።

ሁለተኛው፥ የ”ትምህርት መስፋፋት፣ የሳይንስና የምርምር ነጻነት ምሁሩ አግኝቶ፣ ለፈጣን ለውጥ፣ ለአእምሮና ለቴክኒክ አብዮት” በሰፊው በር በመከፈቱ ነው፤ ብሎ የታሪክ ጸሐፊው ያስረዳል።

ሦስተኛው፥ በእሱ እምነት፣ (ይህቺን ቀጥላ በቅ የምትለውን ቃል አምባገነኖች ፈጽሞ መስማት አይወዱም) “የሕግ በላይነት፣ ነጻ ፍርድ ቤት፣ የዳኞች፣የነገረ ፈጆች፣ የጠበቃዎች መምጣት ነው”፤ይላል። ማለት በሕግ ፊት “የእኔና የአንተ/አንቺም እኩልነት”!

አራተኛውና አምስተኛውን ፣ ስድስተኛውን ጭምር፥ እናንተው ፍላጎት ከአላችሁ፣ መጽሐፉን ጨብጣችሁት እንድትከታተሉት እንጋብዛችኋለን።

የፍርጉሶን መጽሐፍ ከጀርመኑ ጸሐፊ፣ ከኦስቫልድ ስፔንግለርም ከዚያ ከ”..የምዕራቡ ዓለም ውድቀት”/2፣ ከሚለው መጽሐፉ ጋር አንድ አድርገው የሚያዩ ሰዎች አሉ። ግን ሁለቱ መጽሐፎች ፍጹም አንድ አይደሉም። እሱም፣ ምሁሩም በትክክል አንድ አይደሉም፣” ይለያያሉ “ይላል። ፍርጉሶን መሰረታዊ ወደ ሆነው ፣ የአውሮፓ ሥልጣኔ ወደ ተገነባበት ወደ ጠርዞቹ “ድንጋዮች”፣ አንመለስ ብሎ እነሱን ለማስተዋወቅ:- እንግዳ ለሆኑ አንባቢዎቹ ምንድናቸው? ብሎ ይጠይቃል። እንግዲህ መልሱን መጽሐፉ ላይ ተከታትሎ ማንበቡ የእናንተ ፋንታ ነው።

በሚቀጥሉት እትመቶቻችን “በባህልና በሥልጣኔ ” ዙሪያ እስከ ዛሬ ድረስ የተጻፉትን መጻሕፍቶች ተራ በተራ ከመደርደሪያችን እያወጣን በአጭሩ፣ በአጭሩ ፍሬ ፍሬ ነገሮቹን እንዲትመለከቱት እንጋብዛችኋለን።ከዚያም ውስጥ ወደፊት የኦስቫልድ ስፔንግለርም መጽሐፍ -“የምዕራቡ፣ የኦክሲደንት ውድቀት” የሚለው አንደኛው ነው።

“እኛ ማን ነን?” የሚለውን ትልቁን ጥያቄ ሰንዝሮ ግሩም ጥራዝ የጻፈውን፣ የሳሙኤል ሐንትግተንን/3 “ፍሬ ሐሳቦች”( ብዙዎቻችሁ ምናልባት ታውቁታላችሁ) ከብዙ በጥቂቱ በመጀመሪያ እሱን አስቀድመን ሸብ አድርገን እናልፈዋለን። …ለምን አሜሪካ? ለምን ቻይና አይሆንም ? የምትሉ አትጠፉም። ስለ እነሱም ጊዜው ሲደርስ እናነሳለን።

አሜሪካንን የምናስቀድምበት ግን ሌላ ምክንያት አለን። የከርሞ ሰው ይበለን!

————————-

1/ Niall FergusonThe Great Degeneration: How Institutions Decay and Economies Die (2012)

2/Oswald Spengler; The Decline of the West /1922; 1923

3/ Samuel P. Huntington – Who Are We? The Challenges to America’s National Identity (2004)

About ለ አእምሮ / Le'Aimero

አሳታሚው፥ ይልማ ኃይለ ሚካኤል - Publisher:- Yilma Haile Michael, Journalist
This entry was posted in ሌሎች / others. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s