ዓለም – የለም ! አፍሪካ እንዴት ሰነበተች?

africa

ዓለም እንዴት ሰነበተች?

ዓለም – የለም ! አፍሪካ እንደት ሰነበተች? ብለን አንድንድ ጋዜጣዎችን አዚህ አምዳችን ላይ መለስ ብለን እናገላብጣለን።

እንደተለመደው ፣ በዚህ ሳምንት በርካታ የአውሮፓና የአሜሪካ ዕለታዊ ጋዜጣዎች፣ አተኩሮአቸውን እንደተለመደው እንደገና በአፍሪካ ላይ ጥለው፣ ቀለማቸውን በዚያ ላይ በበቂ አፍሰዋል።

ሃማሣኛውን አመት በዛሬው ቀን አዲስ አበባ ላይ ሰለሚያከብረውም „የአፍሪካ አንድነት ማህበረሰብ“ ብዙዎቹ እየተቀባበሉ፣ ይህቺ አህጉር በአለፉት ሃማሣ አመታት ከየት ተነስታ ዛሬ የት እንደደረሰች? አሁን ደግሞ ምን ዓይነት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ችግሮች ፣ ጣጣና መንጣጣ፤ ውስጥ ገብታ እንደምትደፋደፍ፣ አብረው አያይዘው፣እነሱ አትተዋል።

የሁለት መሪዎች ስም በተደጋጋሚ ከፍተኛ ቦታ ይዞ እንደገና ስለእነሱ በበቂ እዚህ ተተርኮአል።

የፈረንሣዩ አገር ጋዜጣ „ጄን አፍሪክ“ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን „…የአፍሪካ አባት ናቸው…“ የሚለውን ግምቱን አምዱ ላይ አስፍሮ፣ ሌሎቹን ሳይረሳ ወደ የጋናው ፕሬዚዳንት ወደ ኩዋሜ ንኩሩማን ተሸጋግሮ፣ እሳቸውንም በሁለተኛ ደረጃ፣ ቅጠሉ ላይ አሰቀምጦአል።

የሞሮኮው ንጉሥ ፣ ንገሥ ሐሰን ሞሪታኒያን ተቃውመው በምሥረታው ላይ ፣ ሌሎቹም እነደጻፉት፣ በቦታው ንጉሡ ተገኝተው እንዳልነበሩ መለስ ብለው አሰታውሰዋል።

„አንድ መንግሥት ፣ አንድ ድንበር፣ አንድ ኢኮኖሚና አንድ ሠራዊት፣…ለዚያች አህጉር …ለተባበረቺውና አንድ ለሆነቺው አፍሪካ፤ ከእንግዲህ ያስፈልጋታል“ ብለው አዲስ አበባ ላይ ፕሬዚዳንት ኮዋሜ ኑኩሩማን ተከራክረው እንደ ነበር፣ የአውሮፓ ጋዜጣዎች ዞር ብለው ታሪኩን መለስ ብለው ተመልክተው ለአንባቢዎቻቸው ጠቅሰዋል።

በሁዋላም እነደምናውቀው፣ እዚህም እንደተጻፈው፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ „በአንድነቱ ምስረታ ብቻ ላይ አፍሪካውያኖቹ አተኩረው፣ በዚህም ላይ ተመካክረው፣ ተስማምተው ድርጅቱን መሥርተው እንዲለያዩ በጠየቁት መሰረት ፣ ህብረቱ ተመስርቶ መሪዎቹ እንደተነሱ…“ „ጄን አፍሪክ“ ወረድ ብሎ አትቶአል።

 

 

 

 

 

ሌሞንድ የተባለው ሌላው የፓሪሱ ጋዜጣ ደግሞ ፊቱን አዙሮ ወደ ኤርትራ ገስግሶ አዚያ ያየውንና የሰማውን „ጉድ“ በዚህ ሳምንት፣ በአወጣው እተሙ ጥሩ አድረጎ በአምዱ ላይ አስፍሮአል።

„….ንፋስና ጸሐይ በየቀኑ የሚመታው ፣ ጣራ የሌለው …“ ጋዜጣው „ ትልቁ ኦፕን ኤየር አምስት ሚሊዮን ሕዝቦች ታጉረው የታሰሩበት ትልቁ የዓለም እሥር ቤት ኤርትራ ነው …“ ብሎ ያንን አገር ለአንባቢዎቹ ሌሞንድ፣ ማስተዋወቁን መርጦአል።

በዚህች ዓረፍተ ነገር ኤርትራን አስተዋውቆም፣ ጋዜጣው ሰተት ብሎ ወደ „ጦረኛው“ ፕሬዚዳንት ወደ እሳቸው ልዩ ባህሪ ፣ወደ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ „ሥራና ድርጊት፣ ድረጊቶች“ ጸሐፊው ገብቶ የሚከተሉትን አረፍተ ነገሮች ቅጠሉ ላይ ለእኛ ለአንባቢዎቹ እንድንመለከተው አሥፍሮአል።

„ከሱዳንና ከየመን“ ጋዜጣው አስታውሶ እንደጻፈው፣“ ከጅቡቲና ከደመኛ ጠላቱ ከኢትዮጵያ ጋር አምባገነኑ የኤርትራ ገዢ „ ሌሞንድ እንዳለው፣ „ጦርነት ከፍቶ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ወታደሮች ሕይወት ኢንዲጠፋ፣ አቶ ኢሳያስ እንዳደረገ …“ ይኸው ጋዜጣ ወረድ ብሎ ዘርዝሮአል።

ይህንን እና ሌሎች ነገሮችንም ፕሬዚዳንቱ አውጥተውና አውርደው፣ በደንብ አስበውበት እንደሚያደርጉም የእራሱን አመለካከትና ግምት ጸሐፊው ከተገነዘባቸውና ከአዳመጣቸው ጉዳዮች ጋር አብሮ አያይዞ አቅርቦአል።

„…ሥልጣናቸውን በኤርትራ ለማጠናከር፣ ሌላ የሌጋሲ፣ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝላቸው ነገር በእጃቸው ሰለሌለ፣ ይህ ብቻ ያዋጣኛል ከሚለው ከንቱ አስተሳሰብ በመ ነሳት ነው፣….“ ብሎም ለአንባቢዎቹ ምክንያቱን ገልጦ ጋዜጣው ዞር ማለቱን መርጦአል።

 

ዋሽንግተን ፖስት የተባለው የሰሜን አሜሪካኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ደግሞ በተራው „የፕሬዚዳንት ኦባማ አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪካቸው አለአብራሪ በሚከንፈው የጦር አይሮፕላናቸው አሜሪካኖች ከድንበራቸው ውጭ ክልል አልፈው ፣ በውጭ አገር በየመንና እና በፓኪስታን አራት ሰው ደብድበው መግደላቸውን አረጋገጡ …“ ብሎ በቅጠሉ ላይ ይህን የመሰለ አዲስ ዜና አስፍሮ ከአንባቢዎቹ፣ ጋር የአደባባይ ሚሥጢር ሆኖ የሰነበተውን ታሪክ፣ እንድናውቀው አድርጎአል። ከየት ተነስቶ ይህ የጦር አይሮፕላን ወደ የመን እንደከነፈ ሳይገልጽልን ጋዜጣው ታሪኩን ቀጭቶ አልፎታል።

ፋይናሻል ታይምስ የተባለው የእንግሊዙ ጋዜጣ ደግሞ ወደ ናይጄሪያ ወርዶ፣ እዚያ ስለተቀጣጠለው የሃይማኖት ጦርነት ቅድሚያ ሰጥቶ“… በሦስት ክፍላተ-አገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዚያ እንደታውጀ ፣ጋዜጣው ለአንባቢዎቹ ማተቱን መርጦአል።

ሌሎቹ፣ የእንግሊዙን ወታድር በጠራራ ጸሐይ አደባባይ ላይ በጩቤና በመክተፊያ ቢላዋ ገዝግዘውና ጨቅጭቀው ስለ ገደሉት ሁለቱ አክራሪ የናይጄሪያ ወጣቶች ዝርዝር ጉዳይ ውሰጥ ገብተው ሰማኑን በርካታ ጽሁፎች አውጥተዋል።

በርሊኑ ጋዜጣ „በርሊነር ዛይቱንግ“ በነገሩ ተገርሞ ፣ ከዚህ በታች የሰፈሩትን ቃላቶች አምዱ ላይ እዚህ አስፍሮአል።

„….እንዴት አንድ ወጣት በሥጋ መክተፊያ ቢላ አንድን ወጣት ወታደር በጭካኔ ገድሎ፣ እጂንም በደም አጨማልቆ ድርጊቱንና ንግግሩን በቪዲዮ እንዲቀረጽለት ሰዎችን ደፍሮ ይጠይቃል…? „ ብሎ አንባቢውን በተራ እዚህ ኢንዲያስቡበት መልሶ ጠይቆ፣ ወደ ሌላ አርዕስት ይሸጋገራል።

„ …የብሪታኒያ ሞስሊሞች ምክር ቤት ግሩም መግለጫ አወጣ „ ብሎ እዚህ ጀርመን አገር ዱስልዶርፍ ከተማ እየታተመ የሚወጣው እንድ „ቬስት ዶቸሳይቱንግ“ የሚባል ጋዜጣ፣ መግለጫውን አድንቆ“….የናይጄሪያ አክራሪ ወጣቶች በዚህ አሳዛኝና አጸያፊ ድርጊታቸው ከእስላሙ ማህበረሰብ እራሳቸውን እንደአገለሉ ምክርቤቱን ጠቅሶ –ይህም ትክክለኛ አቋም ነው“ ብሎ አስተያየቱን አዚህ አረፍተ ነገር ዘግቶአል።

„ ለሁሉም የእስላም ሃይማኖት ተከታዮች በተለይ እዚህ ከአሉበትና ከሚኖሩበት ሕብረተሰብ ተቀላቅለውና ተግባብተው በሰላም አምላካቸውን እያመሰገኑ ከሌሎቹ ጋር ተቻችለው ለመኖር ለሚፈልጉ አማኞች እንደዚህ ዓይነቱ የአረመኔ ሥራ፣ ለእነሱም ቢሆን መዓት እንደወረደባቸው ይቆጠራል።“ ብሎ የኮለኙ ጋዜጣ በሐሳቡ ላይ አስምሮበት አልፎአል።

„ለምን ይጠሉናል?…“ የሚለውን ጥያቄ የበርሊኑ ጋዜጣ አንስቶ ወደ ዝርዝር ሁኔታው ተሸጋግሮአል። „ግለሰቦች አድፍጠው፣ በተለይ የእስላም አክራሪዎች የሚወስዱት ኢ ሰባዊ የጭካኔ ሥራዎች፣ ወደፊት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ስለሆነ፣ በደንብ እንዲታሰብበት…“ ሌላው የበርሊኑ ጋዜጣ „ዲ ታገስሳይቱንግ“ እዚህ የጸታውን ክፍል ጠይቆአል።

 

 

 

ሌሎቹ ዕለታዊ ጋዜጣዎች ፣ ሰሞኑን እዚህ ጀርመን አገርና ኢዚያም ሎንዶን ከተማ ዘገባውን ለዓለም ሕዝብ ይፋ ያደረገውን „የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል „ ወፍራም ጽሑፍ እሱን ቀበል አድርገው ሰፋ ያለ ቦታ ሰጥተው፣ አገላብጠው ለእኛ ለአንባቢዎቹ ማቅረቡን መርጠዋል።

„ የበደልና የግፍ፣ የኣሳፋሪ የጭካኔ ሰነድ..“ በሚለው አርዕስቶቻቸው ሥር ብዙዎቹ ቅጠሎች፣ የሚከተሉትን ሐቆች ከዘገባው ላይ ቦጭቀው፣ ለአንባቢዎቻቸው ሰብሰብ አድርግው እንዲመለከቱት አቅርበዋል።

„ …በአንድ መቶ አሥራ ሁለት መንግሥታትና አገሮች ውስጥ( አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ናቸው ) እሥረኞች በመንግሥት ወታደሮች፣ ይደበደባሉ፣ በጸጥታፖሊሶች ይገረፋሉ፣ ጥዋት ማታ ይሰቃያሉ…“ ይላሉ።

„ በሰማንያ አገሮች ውስጥ ( አሁንም አብዛኛው በአፍሪካ ውሰጥ ነው) አለ አግባብ ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ተገቢ የሆነ ሕጋዊ እንክብካቤ ስይደረግላቸው ፍርደ ገምድል ውሳኔ በጉልበት ይበየንባቸዋል። ከዚያም እሥር ቤት እንዲማቅቁ ይጣላሉ „ ብሎ ዘገባው መንግሥታትን ከሶአል።

…“በአለፈው አመት ብቻ አሥራ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች መንደራቸውን ለቀው ፣አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱም ተደርጎአል። „ አብዛኛዎቹም አፍሪካውያኖች እንደሆኑም ሰነዱ ላይ ሰፍሮአል።

„…አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ አሥራ አምስት ሺህ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች እና ቦታዎች በተፈጠሩ የጦር ግጭቶች ሳቢያ ሕይወታቸውን እንዳጡ…“ ሰነዱን መሰረት አድርገው የአውሮፓ ጋዜጣዎች ጉዳዩን ዘግበዋል።

„ በአንድ መቶ አንድ አገሮችና መንግሥታት ውሰጥ ደግሞ —አሁንም አብዛኛዎቹ የእኛው ጉድ ናቸው– የመናገርና የመጻፍ ፣የመቃወምና የመደገፍ፣ የመተቸትና የመጠየቅ፣ የመምረጥና የመመረጥ፣…መብቶች „ ሁሉም ጋዜጣዎች እዚህ ሰሞኑን እንጻፉት „ በአፍሪካ ተገፎአል።“

„ይህን ሁሉ እኛ በደንብ እናውቃለን የሚለውም ማስረጃ „ አብሮ ታትሞአል።

„…የሰውን ልጆች ሰበአዊና ዲሞክራሲያው መብቶቻቸውን የሚረግጡና የሚያፍኑ መንግሥታት ከእንግዲህ እራሳቸውን ደብቀው በአጥር ግቢያቸው ውስጥ የፈለጉትን ነገር እንደልባቸው በአፍሪካም ሆነ በሌላም አካባቢ ማድረግ አይችሉም …“ የሚለውን የድርጅቱ ተወካይ በርሊን ላይ የወረወሩትን ቃል ፣ ብዙዎቹ ጋዜጣዎች ቀበል አድርገው ሰሞኑን በአወጡት አምዶቻቸው ላይ ግጥም አድርገው አውጥተዋል።

ይህ ዜናም ዛሬ አዲስ አበባ ላይ የአፍሪካ መሪዎች ከደገሱት የፈንጠዚያ ጭፈራ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ሰው ሁሉ፣ እዚህ ያውቀዋል።

አብዛኛዎቹ ከእነ ድርጅቶቻቸው በተከታታይ… ሃያ፤ …ሰላሳና አርባ አመታት በህዝቦቻቸው አናት ላይ ጉብ ብለው እንደሚቀልዱባቸው፣ እዚህ ይታወቃል።

„…አለነጻነት፣ አለነጻ ሰውና አለዲሞክራሲ…አለ ነጻ ዜጋም ….በአንድ አገር ዕድገት የለም፣ ሰላምም የለም!..“ ብሎ አንዴ የጻፈውን ጸሐፊ እንደገና ማንሳት ያስፈልጋል። እሱ ግን ወደ ሌላም ቦታ ይወስደናል።

About ለ አእምሮ / Le'Aimero

አሳታሚው፥ ይልማ ኃይለ ሚካኤል - Publisher:- Yilma Haile Michael, Journalist
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s